የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት 7ኛ ዙር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና መርሐ-ግብር መክፈቻ ሥነ-ስርዓት በጅማ ዪኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
በመርሐ-ግብሩ መክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ሂሩት ድሌቦ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባር አንድ ሰው የህሊናን ፈቃድ ተከትሎ ያለውን ማንኛውንም ነገር ያለስስት ለሌሎች መስጠት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የበጎ ፊቃድ ተግባርን በአግባቡ መጠቀም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማሳደግ የሚቻልበት የፍቅር ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።
“በጎነት ለአብሮነት በሚል መሪ ሐሳብ በሰላም ሚኒስቴር የተጀመረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት መርሐ ግብር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ በዘር ፣ በጎሳ ፣ በሃይማኖትና በሌሎች ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መከፋፈልና ጥርጣሬ በማስወገድ የወጣቶችን የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ ሚናው የጎላ ስለሆነ ለሀገራችን በእጅጉ አስፈላጊ ፕሮግራም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የጅማ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ካምፓስ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር እና የዩንቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ኤፍሬም ዋቅጅራ ብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ስልጠና መርሐ ግብሮችን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሁሉም ዙሮች በመቀበልና በማሰልጠን ለበጎ ሥራና ለሰላም ግንባታ አጋር መሆን ችለናል ብለዋል፡፡
‘በማኅበረሰብ ውስጥ ነን’ የሚለውን የዩኒቨርሲቲያችንን መሪ ቃል በተግባር ያሳየንበት ብሎም የሰላም አምባሳደር መሆናችንን ያስመሰከርንበት ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ከመላ ሀገሪቱ የተወጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ያሳተፈ እና የሰልጣኞቹን ክህሎት ሥነምግባር ፣ አመለካከት ፣ የአካል ብቃት ፣ የሞራል ግንባታ የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሥልጠናው አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲገነዘብ በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር አስተሳሰብ ማሳደግን ያማከለ መሆኑም ተገልጿል።
የተጀመረው የበጎ ፈቃድ ተግባር ወጣቶች ማህኅበራዊ እሴቶችን እንዲያዳብሩ በማድረግ በሀገራችን የሰላም ግንባታ ተግባር ድርሻቸውን እንዲወጡ ከማድረጉም በላይ ማኅበራዊ ትስስራቸውን እንደሚያጠናክርም ተጠቁሟል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የሰላም ሚኒስቴር እና የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዋልታ
