ጠ/ሚ ዐቢይ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ፈጠራዎች ዐውደ ርዕይ ከፈቱ
ሚያዝያ 29/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ፈጠራዎች ዐውደ ርዕይ ከፈቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርና ሚኒስቴር፣ የግብርና ትራስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በመተባበር በሳይንስ ሚዚየም ያዘጋጀውን የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ፈጠራዎች ዐውደ-ርዕይ ነው በይፋ የከፈቱት።
“ከቤተ ሙከራ ወደ አዝመራ” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ የጀመረው አውደ ርዕዩ 70 የውጭና የሀገር ውስጥ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ምርቶቻቸውን እና የግብርና ቴክኖሎጂዎቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።
ዐውደ-ርዕዩ ለሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ የግብርና ውጤቶች ለእይታ የቀረቡበት ነው።
በዐውደ-ርዕዩ የመክፈቻ መርኃ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
ዐውደ-ርዕዩ ከሚያዝያ 29 ጀምሮ ለተከታታይ ሳምንታት ለህዝብ እይታ ክፍት እንደሚሆንም ተገልጿል።




ዋልታ
