ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 3ኛውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር መድረክ በይፋ ከፍተዋል።
ውድድሩ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ‘ክህሎት ለተወዳዳሪነት’ በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣይ አምስት ቀናት የሚቀጥል ነው ተብሏል።
በውድድሩ የፈጠራ ስራዎች ዐውደ ርዕይ፣ ፓናል ውይይትና ሌሎች መርሐ-ግብሮች እንደሚኖሩ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ÷ኢትዮጵያን ለመለወጥ መፍትሔ ተኮር መሆን የግድ ነው ብለዋል።
የተለያየ ብቃት እና ችሎታ ያላቸው ወጣቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ያቀረቡበት ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ዛሬ መጀመሩን ጠቅሰው÷”እንበርታ፣ እንፍጠር፣ ፈተናን ለማለፍ መፍትሔ ላይ እናተኩር” ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ለማበልፀግና ሁሉንም ዘርፍ ለማዘመን ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ዘርፎች የግብዓት ችግር ስለሌለ ፈጠራና ክህሎትን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የፈጠራ ባለሙያዎች በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ሳይበገሩ ፈተናዎችን እንደመስፈንጠሪያ ተጠቅመው ውጤት ተኮር ስራዎች ላይ አበክረው እንዲሰሩ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዕለቱ በቀረቡ የፈጠራ ስራዎችም ትልቅ ተስፋ ሰጭ ፈጠራ ስራዎችን እንደተመለከቱ ገልፀው÷ ሚኒስቴሩ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
ፋና
