በትግራይ ክልል ሀውዜን አቅራቢያ የሚገኙት የገርዓልታ ተራሮች ለማመን የሚከብዱ ተፈጥሯዊ አቀማመጦች አሏቸው።እነዚህን ተራሮች ታዳያ የአካባቢው ማህበረሰብ ለመንፈሳዊ መዳረሻነት አለት ፈልፍሎ ያነጻቸው ከበርካታ ክፍለ ዘመናት በፊት እንደነበር ድርሳናት ያመለክታሉ።እነዚህ ተራሮች ላይ መድረስ ታዲያ ጀብደኝነትን ጭምር የሚጠይቅ ነው ይላሉ ወደ አካባቢው ጎራ ብለው የተመለሱ።
አካባቢው መሰረተ ልማት ያልደረሰው በመሆኑ እምብዛም ያልተጎበኙ ወይም ያልታወቁ በርካታ አብያተክርስቲያናትም ጭምር መገኛ ነው፡፡
ጎብኚዎች ከተራራ ተፈልፍለው የተሰሩ የገርዓልታ አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት ተራራውን “እየቧጠጡ” መውጣት ይጠበቅባቸዋል :: በአካባቢው ያሉ እናቶች ለዘመናት ያህል አዲስ የተወለዱ ህፃናትን በቤተክርስቲያን ስርዓት ‘ክርስትና ለማስነሳት’ ተራራውን በመውጣት ስርዓቱን መካፋል ይጠበቅባቸዋል፤ይህ ድርጊትንም የአካባቢው ማህበረሰብ ሲፈፅመው ከትውልድ ትውልድ ተሻግሮ አሁን ላይ ደርሷል።
በገርዓልታ ተራራማ ስፍራዎች ሊጎበኙ ከሚገባቸው ስፍራዎች ጥቂቶቹ ሲሆኑ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ቅርስ የሚያሳዩ እንዲሁም ቱሪስቶችን በቀላሉ የሚስቡ ስፍራዎች አካባቢውን አድምቀውታል፡፡
በውጭ ቱሪስቶች ብቻም ሳይሆን በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሊጎበኙ የሚገባቸው እንደሆኑ አካባቢውን የሚያውቁትና ጎብኝተው የተመለሱ ይመክራሉ፡፡
እነዚህን አዕምሮን እና መንፈስን የሚያድሱ የገርዓልታ ተራሮችና ቅርሶቹን ለመጎብኘት የገርዓልታ ሎጅ ያለ ቢሆንም ከዚህ ላቅ ባለ መልኩ አካባቢው በመሰረተ ልማት ቢደምቅ ተፈላጊነቱን ከፍ ማድረግ ይቻላል የሚሉም ብዙ ናቸው። ይህን ታሳቢ በማድረግ ይመስላል በገበታ ለትውልድ ከሚገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ተደርጎ መመረጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ያስታወቁት።
ገርዓልታ በገበታ ለትውልድ ሲለማ አካባቢው አስደማሚ የቱሪዝም ማዕከል ከሚሆኑ የተመረጡ ኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ምንጭ፡ ኢዜኣ
