ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ “ለአገር እና ለሕዝቦቿ አኩሪ ስራ የሰሩ ” ብሎ ለሰየማቸው ለአምባሳደር መሐሙድ ድሪር የክብር ዶክትሬት አበረከተላቸው።
ዩኒቨርሲቲው 1 ሺህ 211 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል 382ቱ ሴቶች ሲሆኑ ተመራቂዎቹ 248 በድህረ ምረቃ እንዲሁም 963ቱ በቅድመ ምረቃ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በምርቃቱ ስነ ስርዓት ላይ አምባሳደር መሐሙድ ድሪር “ለአገር እና ለሕዝቦቿ አኩሪ ስራ የሰሩ ” ብሎ ለሰየማቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የክብር ዶክትሬት አበርክቶላቸዋል።
አምባሳደር መሐሙድ ኢትዮጵያ በራሷ ሃብት የመጠቀም ሙሉ መብቷ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ አከናውነዋል ሲል ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።
በሰላም አደራዳሪነት በመሳተፍ ለአፍሪካውያን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጾ በዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ የኢትዮጵያ መብት፣ ፍላጎትና ጥቅሞች የሚያስከበር ውጤታማ ግንኙነት በዲፕሎማቲክ ዘመናቸው ገንብተዋል ብሏል።
በተጨማሪ ኢትዮጵያ የቀደመት ስልጣኔ ታሪክ ባለቤት መሆኗን የሚያስመሰክሩትን ቅርሶች ወደ ሀገር በማስመለስ ሚና መጫዋታቸውንም አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብት መፋጠን፣ ለዘላቂ ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ፣ የሕዝብ የእርስ በእርስ ግንኙነትና መስተጋብር እንዲጠናከር እንዲሁም ዜጎች የልማቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል ነው ያለው ዩኒቨርሲቲው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለሰጣቸው ክብር እና ማዕረግ የተሰማቸውን ደስታና ምስጋና ገልጸው በቀጣይም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከመቼውም ጊዜ በላይ በቀሪ ዘመናቸው ለማገልገል እንደሚተጉ ገልጸዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ፤ አምባሳደር መሐሙድ ለተመራቂዎቹ የደስታ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ተመራቂዎች በቀጣይ በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት አገራቸውን ወደ ተሻለ እድገት ለማድረስ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ አበክረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
