የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለትግራይ ክልል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ዛሬ ወደ ትግራይ ክልል መላኩ ተገለጸ።
ድጋፉ 11 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲሆን ቀሪው አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ኮምፒዩተሮች እና የህክምና መሳሪያ ቁሳቁስ መሆናቸው ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ልዩ አማካሪ ውብአየሁ ማሞ በዛሬው ዕለት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዩኒቨርሲቲው መሰል ድጋፎችን በቀጣይነት ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው በምርምርና ቴክኖሎጂዎች ረገድም በመልሶ ማቋቋሚያ ስራዎች ላይ የራሱን እገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።
ዋልታ
