ሚስተር ቢስት ይባላል። ብዙዎቻችሁ ታውቁት ይሆናል። የመዝገብ ስሙ ጄምስ ስቴፈን ዶናልድሰን ነው።
በዩቲዩብ ዓለም የገነነ ነው።156 ሚሊዮን ‘ሰብስክራይበሮች’ አሉት።
ወደ ዩቲዩብ አቅንተው የአንድ ሰው ገፅ ‘ሰብስክራይብ’ የምትል ጠቋሚን ሲጫኑ የዚያ ሰው ቋሚ ደንበኛ ሆኑ ማለት ነው።
ሚስተር ቢስት በግለሰብ ደረጃ በርካታ ተከታዮች [ሰብስክራይብ አድራጊዎች] ያሉት ቁንጮ ዩቲዩበር ነው፤ ይላል ዩኤስቱዴይ።
ይህ ግለሰብ የሚታወቀው በተለያዩ መንገዶች ለማያውቃቸው ሰዎች ረብጣ ብር በማደል ነው።
ቲሲሪስ የተሰኘው የሕንድ ሙዚቃ ስቱዲዮ ደግሞ 241 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ቁጥር አንድ የድርጅት ዩቲዩብ ገፅ ነው።
ሚስተር ቢስት በ2021 (እአአ) 54 ሚሊዮን ዶላር ከዩቲዩብ አግኝቷል ይላል ፎርብስ መፅሔት።
በጠቅላላው በ2021 ዩቲዩበሮች 300 ሚሊዮን ዶላር ወደ ኪሳቸው አስገብተዋል።ይህ ገቢ በዋናነት ከማስታወቂያ የሚገኝ ነው።
ዩቲዩብ በአሜሪካ እና ሕንድ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማስታወቂያ በማይሄድባቸው አገራትም ለዩቲዩበሮች ገቢ ማግኛ አማራጭ ሆኗል።
ግዙፉ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ማጋሪያ አሁን 500 ሰብስክራይበር እና 3 ሺህ የዕይታ ሰዓት ካለዎ ገቢ ማግኘት ይቻላል ብሏል።
ይህ ምን ማለት ነው? ከዩቲዩብ የሚገኘው ገቢ እንደ ኢትዮጵያ ወዳሉ አገራት እንዴት ይመጣል?
ዩቲዩብ ‘ፓርትነር ፕሮግራም’
ቀድሞ የዩቲዩብ ገፅ ከፍተው ገቢ ለማግኘት ቢያንስ 1 ሺህ ደንበኛ [ሰብስክራይበር] መሰበሰብ ይጠበቅብዎ ነበር።
አሁን ግን ዩቲዩብ ይህ ወደ 500 ዝቅ እንዲል አድርጊያለሁ ይላል።የዕይታ ሰዓቱም ወደ ሦስት ሺህ ዝቅ ብሏል።
ለጊዜው ይህ የተፈቀደው በዩናይትድ ስቴትስ፣ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ በካናዳ፣ በታይዋን እና በደቡብ ኮሪያ ላሉ ተጠቃሚዎች ነው።
ዩቲዩብ ትንሽ ከታገሳችሁኝ ይህን ሥርዓት በቅርቡ ለበርካታ አገራት አዳርሳለሁ ብሏል።
ዩቲዩበሮች ከተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉት ዩቲዩብ ፓርትነር ፕሮግራም በተሰኘው ማዕቀፍ ነው።
ዩቲበኞች የዚህ ማዕቀፍ ተጠቃሚ ለመሆን 500 ሰብስክራይበር ሊያሰባስቡ እና በሦስት ወር ቢያንስ ሦስት ጊዜ ቪድዮ ሊጭኑ ይገባል።
አሊያም 3 ሺህ ሰዓት ቪድዮዎቻቸው ሊታይ ይገባል። ካልሆነም 3 ሚሊዮን የዩቲዩብ ሾርት ዕይታ ማጋበስ አለባቸው።
ዋይዲ ቶም [YD TOM] በተሰኘ የዩቲዩብ ገፅ የሚታወቀው ይድዲያ ቶማስ 106 ሺህ ሰብስክራይበሮች አሉት።
በዩቲዩብ እንዴት ገቢ ማግኘት ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ ተንትኖ ይመልሳል።
“ለምሳሌ አንድ የ10 ደቂቃ ቪድዮ ለጠፍክ እና 30 ሺህ ጊዜ ታየ እንበል” ይላል ይድዲያ።
“ስለዚህ ይህንን የ10 ደቂቃ ቪድዮ በ30 ሺህ አስልቶ ወደ ሰዓት መቀየር ነው።ይህን ሥራ ዩቲዩብ ራሱ ነው የሚሠራው። ነገር ግን 10 ደቂቃ ሙሉ ሰው አያየው ይሆናል።”
እንደሱ ገለፃ የ10 ደቂቃ ተለጠፈ ማለት ሰው ሙሉን ያየዋል ማለት አይደለም።አንዳንድ ሰው 5 ደቂቃ ተመልክቶ በቃኝ ሊል ይችላል።
ነገር ግን ዩቲዩብ ‘አቬሬጅ ቪው ዱሬሽን’ የተሰኘ ቴክኖሎጂ አለው።ይህ በአማካይ ቪዲዮው ምን ያክል ታየ የሚለውን የሚተምን ነው።
ይድዲያ ዩቲዩበሮች ገቢ ለማግኘት ያለመታከት ብዙ ቪዲዮዎችን እንዲጭኑ ይመክራል። ነገር ግን በአንድ ቪዲዮም በርካታ ዕይታ ሊገኝ ይችላል።
“ለምሳሌ እኔ በአንድ ‘የፕራንክ’ ቪዲዮ ጭኜ ብዙ ሰው ያየልኝ። ሰላሳ፤ አርባ ሺህ ታየልኝ። አማካይ ዕይታው 4 ደቂቃ ነበር፤ ነገር ግን ሞላልኝ።”
የዩቲዩብ ይሁንታን ማግኘት
ይዲድያ ‘ሱፐር ቻት’ ስለተሰኘው የዩቲዩብ ገፅም ለቢቢሲ አማርኛ ይገልጻል።
‘ሱፐር ቻት’ ማለት ልክ እንደ ቲክቶክ ሰብስክራይበሮች ስጦታ የሚሰጡበት ነው።ለምሳሌ አንድ ሰው ‘ታንክስ ካርድ’ ብሎ 100 ዶላር ስጦታ ሊሰጥህ ይችላል።
ዩቲዩብ ይዘት አዘጋጆችን ለማበረታታት ቀድሞ 1 ሺህ ሰብስክራይበር እና 4 ሺህ የዕይታ ሰዓት የነበረው አሁን ወደ 500 ተከታዮች እና 3 ሺህ የዕይታ ሰዓት ዝቅ ማለቱን ይናገራል።
ነገር ግን ይህ ለውጥ በአሁኑ ጊዜ በተወሰኑ አገራት ውስጥ ብቻ ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፣ በቀጣይ ሌሎችንም አገራት እንደሚያካትት ተገልጿል።
