የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኮሎራዶ ግዛት የአሜሪካ አየር ኃይል አባላት የተመራቂዎችን ስነ-ስርዓት ላይ መድረክ ላይ ሳሉ ተደነቃቅፈው ሲወድቁ ታዩ።
በአሜሪካ ታሪክ በዕድሜ ትልቁ መሪ የሆኑት የ80 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ከወደቁበት ለመነሳት የሰዎች እርዳታ አስፈልጓቸዋል።
ከወደቁበት ሲነሱ ጉዳት የደረሰባቸው የማይመስሉት ባይደን፤ ተደናቅፈው ከመውደቃቸው በፊት የ921 ተመራቂዎችን እጅ እየጨበጡ ለ90 ደቂቃ ያክል መድረክ ላይ ቆመው ነበር።
ከክስተቱ በኋላ የዋይት ሃውስ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ባይደን ‘ደኅና ናቸው” ብለዋል። ዳይሬክተሩ ቤን ላቦለት በትዊተር ገጻቸው ፕሬዝዳንቱን አደናቅፎ የጣለው መድረኩ ላይ ተቀምጦ የነበረ በአሸዋ የተሞላ ጆንያ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደንም በዛው ምሽት ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ በኋላ ‘በአሸዋ በተሞላ ጆንያ ተጠልፍኩ’ ሲሉ በቀልድ መልክ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
ፕሬዝደናቱ ሲወድቁ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል የንግግር ጽሑፋቸውን የሚያነቡበት መስታውትን ደግፎ ለማቆም የተቀመጠ ጥቁር ጆንያ አደናቅፏቸው ሲወድቁ አሳይቷል።
ፕሬዝዳንቱን ከወደቁበት በሁለት የአየር ኃይል አባላት እና በጠባቂዎቻቸው ድጋፍ ሲነሱ ጠልፎ ወደጣለቸው ጆንያ በጣታቸው ሲያመላክቱ ነበር።
ከምርቃት ስነ-ስርዓቱ በኋላም ባይደን ለደኅንነታቸው ማረጋገጫ ለመስጠት በሚመስል መልኩ በሶምሶማ ወደሚጠብቋቸው መኪኖች አምርተዋል።
ባይደን ከእአአ 2020 ጀምሮ አሜሪካን እየመሩ ይገናኙ። ፕሬዝዳንቱ የዓለማችንን ኃያል አገርን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ዳግም ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ እንደሚወዳደሩ ይፋ አድርገዋል።
ተቀናቃኝ እና ተቺዎቻቸው ግን ፕሬዝዳንቱ ለሁለተኛ ዙር አገሪቱን ለማስተዳደር ዕድሜያቸው አይፈቅድም ይላሉ።
በቅርቡ የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች አብዛኛው ድምጽ ሰጪ አሜሪካውያን የፕሬዝዳንቱ የዕድሜ መግፋት እንደሚያሳስባቸው አሳይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቀጣዩን የአሜሪካ ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ሁለተኛ ዙር ስልጣናቸውን የሚረከቡት በ82 ዓመታቸው ይሆናል።
ባይደን በአደባባይ ሲደነቃቀፉ ሲታዩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከዚህ ቀደም ከብስክሌታቸው ላይ ሲወድቁ እንዲሁም ኤየር ፎርስ ዋን አውሮፕላን ለመሳፈር ደረጃ ሲወጡ ተደነቃቅፈው ሲወድቁ ታይተዋል።
