በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪዎችን ትሥሥር ሊያጠናክር በሚችል ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከአስረጂዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም ከከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና፣ ምርምር ተቋማት እና ኢንዱስተሪ ጋር ያለውን ትሥሥር በማጠናከር በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ረቂቅ አዋጁ ሊያግዝ እንደሚችል ተጠቁሟል።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ ችግር ፈቺ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች በቅንጅት እና በትብብር እንዲሠሩ ለማስቻል ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር እና ማኅበራዊ ጉድኝት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሰለሞን ቢኖር በበኩላቸው፣ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ኢንዱስትሪዎች ምርታማነት እንዲጨምሩ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማጠናከር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ ረቂቅ አዋጁ የከፍተኛ ትምህርት የምርምር ውጤቶችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የእውቀት ሽግግር ጭምር ለማስገኘት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ በረቂቅ አዋጁ ያሉ አሠራሮችን በግልፅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር) ኢንዱስትሪዎችን ከተቋማት ጋር በማስተሳሰር እንደ ሀገር በኢኮኖሚው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ታሳቢ በማድረግ በረቂቅ አዋጁ ተጠያቂነትን እና ኃላፊነትን በግልፅ ማስቀመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከንድፈ-ሐሳብ ይልቅ በተግባር ትምህርት የተደገፈ እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ ኢንዱስትሪዎችን በግብአትነት ለመጠቀም በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም ማመላከታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ የተሰጡትን አስተያየቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስተካክሎ በሦስት ቀናት ውስጥ ማቅረብ እንዳለበት ረቂቅ አዋጁ የተመራላቸው የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳች እና የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች አሳስበዋል።
ኢዜኣ
