የአሜሪካ መንግሥት ከትግራዩ ጦርነት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ አገራት ከሚሰጠው የቀረጥ ነጻ ንግድ ዕድል (አጎዋ) መሰረዙን ያስታወቀው በጥቅምት 2013 ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነጻ እድሉ ያስወጣት ጦርነት በሠላም ስምምነት ከተቋጨ ከ10 ወራት ገደማ በኋላ ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ዕግድ ይነሳ ወይስ ፀንቶ ይቆይ በሚለው ላይ የመጀመሪያውን ውይይት አድርጓል፡፡ በጉዳዩ ላይ የሚመክረው በአሜሪካ የአጎዋ ንዑስ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቱን ያካሄደው ሰኞ ሐምሌ 17፣ 2015 ነው፡፡
ኮሚቴው ማካሄድ ከጀመረው የባለድርሻ አካላት ውይይት በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የገበያ ዕድሉ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል ወይም አይገባም የሚለውን አገር አስመልክቶ ምክንያታዊ ድጋፍ ወይም ቅሬታ በጽሑፍ እንዲልክ ይፈቀድለታል፡፡ ኮሚቴውም በሚያካሂደው ግምግማ ይህንኑ በግብዓትነት ይጠቀምበታል።
በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነትን በተመለከተ የድጋፍና የተቃውሞ ክርክሮችን በጽሑፍ የተቀበለ ሲቀበል በኢትዮጵያ ላይ ድጋፍና ቅሬታቸውን ለማሰማት የጠየቁ አካላትን አድምጧል።
በተቃውሞ ጎራ ከተሰለፉት መካከል ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እድሉን ልትነጠቅ ይገባል በሚል ተከራክሮ ውጥኔን አሳክቻለሁ ሲል የነበረውና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የፖሊሲ አማካሪና ተሟጋች ኩባንያው ቮን ባተንሞንታግ ይገኝበታል፡፡ ይህ ኩባንያ በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ቬናብል እና ሜርኩሪ ፐብሊክ አፌይርስ የተሰኙ የሎቢ ኩባንያዎችን ሲቀጥር መቀመጫውን አሜሪካ አሌክሳንድሪያ ባደረገው ትግራይ ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ኤንድ ኮሚኒኬሽን ከመንግሥት በተቃርኖ እንዲከራከር የተቀጠረ ነበር፡፡ ኩባንያው ሰኞ በተካሄደው ውይይት ኢትዮጵያ አሁንም ከአጎዋ ታግዳ መቆየት አለባት ለማለቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ አሁንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም አላቆመም ሲል ተከራክሯል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ እንደ ቮን ባተንሞንታግ ሁሉ ትግራይ አክሽን ኮሚቴ እና ቅንጅት ለአፍሪካ አድቮኬሲ የተባሉ የመብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚነት ታግዶ እንዲቆይ ጠይቀዋል።
በአንጻሩ የአሜሪካ አልባሳትና ጫማ ማኅበር፣ ሳን ማር ኮርፖሬሽን፣ ዘ ቻይልድ ፓላስና የአጎዋ ጥምረት የሚባሉ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ መሻሻል በማሳየቱ ዕግዱ ይነሳላት ብለዋል፡፡
የአጎዋ ኮሚቴ ኢትዮጵያና ሌሎች የሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ለአጎዋ ተጠቃሚነት ብቁ መሆናቸውን ለመለየት የጀመረውን ግምገማ አጠናቆ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
አምባ ዲጂታል
