የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ኮፐንሀገን ዴንማርክ አዲስ በረራ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።
በበረራው ማስጀመሪያ መረሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ በተያያዘው የእድገት መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እያሰፋ ይገኛል ብለዋል።
አየር መንገዱ በሳምንት አምስት ጊዜ ወደ ከተማዋ የመንገደኞች በረራ እንደሚያደርግ ዋና ሰራ አሰፈፃሚ መስፍን ጣሰው ያስታወቁ ሲሆን፣ በአውሮፓ በተለይም በስካንዲኒቪያ አገራት ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ወደ ዴንማርክ የሚያደርገው በረራ በአውሮፖ 21ኛ መዳረሻው ሲሆን ዓለም አቀፍ በራራ መዳረሻውን 134 የሚያደረሰው ይሆናል።
ይህኛው በረራም አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት የሚያስችለው መሆኑን ዋና ሰራ አሰፈፃሚው ገልጸዋል።
የአየር መንገዱ በረራ በዴንማርክና ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ጋር የማስተሳሰር እድል የሚሰጥ መሆኑንም የዴንማርክ ኤምባስ አማካሪ ሲብ በርዝ ገልፃዋል።
ኢዜኣ
