የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የጋምቤላ ክልል አካባቢዎች ሲከሰቱ የቆዩ የትጥቅ ግጭቶችን፣ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶችንና አጠቃላይ የጸጥታ ችግሮችን እና በዚህ ሳቢያ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ተጎጂዎችን፤ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች እንዲሁም የክልሉን የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎችን በማነጋገር ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በላከልን መግለጫ አሳውቋል።
በተለይ ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ላለው የጸጥታ ችግር መነሻ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተወሰነ ነዋሪዎች መካከል የተነሳ አለመግባባት መሆነ ማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ይሄው አለመግባባት በፍጥነት ወደ ብሔርን መሠረት ያደረገ ውጥረት እንደተሸጋገረ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
ይህንኑም ተከትሎ የተለያየ ብሔር ታጠቂ ቡድኖች በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግ ወረዳ፤ በጋምቤላ ከተማ ብሔር ብሔረሰቦች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እና በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሰፈሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት በርካታ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ደርሷል።
ኢሰኮ በጸጥታው ችግር ምክንያት ገና ወደ አካባቢዎቹ በአካል ደርሶ ምርመራ ለማድረግ ያልቻለ ቢሆንም፣ ነዋሪዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ መንደሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የወደሙ መሆናቸውን አስረድተዌ።
ጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን በሚመጡ ታጣቂ ቡድኖች በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ በክልሉ በሚኖሩ ብሔሮች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስ መሆኑ እንደሚታወቅ ኢሰመኮ በመግለጫው አመልክቷል።
ክልሉ ወደ 350 ሺህ የሚጠጉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን በስምንት የተለያዩ ካምፖች ያስተናግዳል።
ከሁለት ወራት በላይ ለዘለቀው የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ችግር እና በክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በመድረስ ላይ ያሉ ግጭቶች ተሳታፊዎችን በተመለከተ ተጎጂዎችም ሆነ የክልሉ የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎች የተለያዩ ብሔር ታጣቂ ቡድኖችን ኃላፊነት ይጠቅሳሉ።
በአንዳንድ አካባቢዎች የክልሉ ኑዌር ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ በሌላ አካባቢ የአኝዋ ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች እና በአንዳንድ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ አንደሚኖሩ የተገለጸ ሰዎች ጭምር በግጭቶቹ ተሳታፊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
እነዚህ ጥቃቶች እና ግጭቶች በአብዛኛው ብሔር ተኮር ሲሆኑ በሌላ በኩል ግጭት የሚደርስባቸውን አካባቢዎች ያለ የብሔር ልዩነት ሁሉንም ነዋሪዎች አካባቢውን ሸሽቶ ለመፈናቀል፣ ለንብረት ውድመት እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ያጋለጠ ነው ሲል ኢሰመኮ አመልክቷል።
የክልሉ ጸጥታ ሁኔታ በነዋሪዎች ላይ ያደረሰው ከፍተኛ ጉዳት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰትም የመንግሥትን ተጨማሪ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አስገንዝቧል።
(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)


