የአፍሪካ ሕብረት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በሕብረቱ ኮሚሽን የተዘጋጀው ስብሰባ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ የብዝሃ ህይወት አለም አቀፍ ስምምነት፣ የኮፕ-15 የተባበሩት መንግስታት የብዝሀ ሕይወት ስብሰባና በ19ኛው ንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት እንስሳትና እጽዋት ላይ ጉዳት ላለማድረስ የተደረገ ስምምነት ስብሰባ ውጤቶች ትግበራ ላይ ያተኮረ ነው።
ብዝሃ ሕይወት በአፍሪካ ለቱሪዝም፣ ለመድኃኒት (ፋርማሲዩቲካል) ኢንዱስትሪ እና ንግድ ዘርፍ ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት የዘላቂ አካባቢ ጥበቃና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሀርሰን ኒያምቢ ገልጸዋል።
ከብዝሃ ሕይወት ማህበረሰብ በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ አለመሆን፣ ሕገ-ወጥ ንግድ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የዓለም የብዝሃ ሕይወት ስብሰባ ውጤቶችንና ስምምነቶችን በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በብዝሃ ሕይወት ላይ ትኩረት ያደረጉ መርሐ-ግብሮችን፣ የእንስሳትና እጽዋት ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የተዘጋጀውን ስትራቴጂና ቀጣይነት ያለው የደን አስተዳደር ማዕቀፍን መተግበር እንደሚያስፈልግ ነው ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።
የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ አውሬሊ ጎዴፍሮይ አፍሪካ የብዝሃ ሕይወትና አካባቢ ጥበቃ ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ለአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዓለም አቀፍ ትብብርና ጥምረትና የገንዘብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።
የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ አየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዳይሬክተር ጂን ፓል በበኩላቸው አገራት ቀጣይነት ያለው የብዝሃ ሕይወት እንዲኖር እያከናወኑ ያለውን ተግባር ያነሱ ሲሆን ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።
በባለሙያዎች ደረጃ የተጀመረው ስብስባ እስከ ነገ ይቆያል።
በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረገው ስብስባ ከነገ በስቲያ የሚጀመር ሲሆን በባለሙያዎች ደረጃ በቀረቡላቸው አጀንዳዎች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢዜኣ
