የአፍሪካ እና ሩስያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በላቀ መልኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቻም ኡጋላ ገለጹ።
የአፍሪካ ሀገራትን ታሪካዊና የተፈጥሮ መስህቦችን የሚያስቃኙ እውነታዎችን በማካተት የተዘጋጀው የአፍሪካ-ሩስያ አውደ-ርዕይ በሩስያ ተከፍቷል።
አውደ-ርዕዩ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ለጎብኝዎች ክፍት ይሆናልም ተብሏል።
በአውደ-ርዕዩ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቻም ኡጋላ ኡርያትን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ በአፍሪካና ሩስያ ግንኙነት ላይ የሚሰሩ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተወካዮችና በሥልጠና ላይ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ጋዜጠኞች ታድመዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አምባሳደር ቻም ኡጋላ የአውደ-ርዕዩን አስፈላጊነት በመጥቀስ የአፍሪካና ሩስያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በላቀ መልኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካና ሩስያን ግንኙነት በሚዲያው ዘርፍም በማጎልበት በተዛባ መልኩ የሚገለጸውን የአፍሪካ ትርክት በመለወጥ እውነታውን ለዓለም ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካና ሩስያ ግንኙነት የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው መሆኑን ጠቅሰው በፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ወቅትም ሩስያ የአፍሪካ ሁነኛ አጋር ሆና መዝለቋን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ስፑትኒክ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የአፍሪካና ሩስያን ግንኙነት ለማጠናከር የባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ጭምር የጀመረውን ጥረት አድንቀዋል።
በተለይም ስፑትኒክ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ለመክፈት በሂደት ላይ በመሆኑ ለመላው አፍሪካ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አምባሳደር ቻም ገልፀዋል።
በተያያዘ ዜና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና ዕውቁ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ቀን በሩስያ የውጭ ስነ-ጽሑፍ ማዕከል በዛሬው ዕለት ታስቧል።
ሁነቱ በሩስያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ጀፍ ዙሁክሉ ማክቱካ ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት ተከናውኗል።
በዚሁ መርኃ ግብር ላይ አምባሳደር ጀፍ ዙሁክሉ ማክቱካ ባስተላለፉት መልዕክት የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ የትግል መርህ ዓለም አቀፉ እሳቤን የያዘ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኔልሰን ማንዴላ የተሻለ ዓለም የመፍጠር ጥረት በማስቀጠል በዓለም ላይ የነፃነት፣ እኩልነትና የፍትሕ እሴትን ማስቀጠል ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
