የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ27ኛ ዙር ያሠለጠናቸውን የመደበኛ እና አድማ ብተና የፖሊስ አባላትን አስመረቀ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ27ኛ ዙር ያሰሠጠናቸውን የመደበኛ እና አድማ ብተና የፖሊስ አባላትን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ለፖሊስ አባላቱ የሥራ መመሪያ በመስጠት ወደ ሥራ አሰማርተዋል።
“መጪው ጊዜ ሕዝባችሁን በቅንነት እና በታማኝነት የላቀ አገልግሎት የምትሰጡበት እንደሚሆን እምነት አለኝ” ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ፖሊሶቹ ወደ ተግባር ሲገቡ ሕዝባቸውን በእኩልነት በማገልገል የማይለካ ክብር እንደሚያገኙም ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፣ ከራስ በላይ ሕዝብን በማስቀደም በማንኛወም ቦታ እና ሁኔታ በቅንነት፣ ሁሉንም በፍቅር በእኩልነት በማገልገል ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት፣ ከብሔር ወገንተኝኘት በመጠበቅ በታማኝነት ማገልገል ሁሌም መዘንጋት የሌለባቸው ተቀዳሚ ተግባራቸው እንዲሆን አሳስበዋል።
ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ በከተማዋ የሚፈፀሙ ውስብስብ ወንጀሎችን በመረዳት ቀድመው ለማክሸፍ በአካልም ሆነ በሥነ ልቦና ጠንካራ እንዲሆኑ አዳዲስ ፖሊሳዊ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸው ተጠቁሟል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ፣ የከተማ አስተዳደሩ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ አካዳሚ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር መኮንን አሻግሬ እንዲሁም በኮሚሽኑ ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።










ኢዜኣ
