Cyber Power Tigray Media (CPT media )

ሳይበር ፖወር ትግራይ ሚድያ – ነፃን ህዝባውን ሚድያ እዩ!


Follow us on:
አማርኛ ዜና
0

የአማራ ክልል ወቅታዊ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታዎች ላይ የሚመክር ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው


የአማራ ክልል ወቅታዊ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታዎች ላይ የሚመክርና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ መድረኩን አስመልክቶ እንደገለፁት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የሰላም ችግር በጋራ ተወያይቶ መፍትሄ ለማምጣት ያለመ ውይይት ነው።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እና ህብትና ንብረት የማጥፋት ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የጸጥታ ችግሩ በተለያዩ አካባቢዎች የልማትና የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመግታት የክልሉን ህዝብ ወደባሰ ችግር ውስጥ እያስገባው መሆኑን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም እየተስተዋለ ያለውን ችግር በሰከነ መንገድ ለመፍታት ከክልሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየትና መመካከር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።

አቶ ግዛቸው እንዳሉት ውይይቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሄዎችን በጋራ በማስቀመጥ የተጀመሩ የልማትና የለውጥ ስራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያግዝ ነው። ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ተወያይቶ መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ላለው ሥራ የሚኖራቸው ሚና የጎላ መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ “በመድረኩም ችግሩን ለመፍታት የሚረዱ ግብአቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።

በውይይቱ ላይ በክልሉ ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ከ400 በላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ሌሎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *