የአማራ እና ትግራይ ክልል ሕዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የተመራ የልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት ባሕርዳ ከተማ መግባቱ ይታወሳል።
ልዑካኑ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ ከአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጌታቸው ረዳ፣ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ በተወሰደው የፖለቲካ ቁርጠኝነት የጦርነት ምዕራፍ ተዘግቷል፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም ተጀምሯል፤ ይህንን በማጠናከር ለሕዝቦች ሰላም እና የቀደመ አብሮነት መጠናከር እንሠራለን” ብለዋል።
በጦርነቱ ሞት፣ የአካል ጉዳት እና መፈናቀልን ጨምሮ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳዳሩ፤ ለደረሰው ጉዳት ከመቆጨት ባለፈ ሕዝብ የሚፈልገውን ሰላም ለማምጣት እየሠራን ለመሆኑ ይህ ጉዞ ማሳያ ነው።
“የሕዝባችን ምኞት ሰላም እና ሠርቶ መኖር ነው፤ ለዚህ ውጤታማነትም ይልቃል ከፋለ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አደንቃለሁ” ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የትግራይ ሕዝብ ለአማራው ወንድሙ መሆኑን ገልጸው፣ “የአማራ የሕዝብ ፍላጎት ያለሰላም ሊሟላ አይችልም፤ የተጀመረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን እና እንዲፀና ሕዝባችን ዝግጁ ነው” ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ የሁለቱን ሕዝቦች ወደቀደመው አብሮነቱ መመለስን፣ ትራንስፖርት እና የንግድ ግንኙነትን ማስጀመርን ጨምሮ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ይበጃሉ ያሏቸውን ጥያቄዎች አንሥተዋል።
“የሰላም በር ተከፍቷል” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሮቹ፣ የሕዝቡን ግንኙነት እና ትሥሥርን የሚያጠናክሩ የትራንስፖርት እና ንግድ መሰል ግንኙነት በቅርብ እንደሚጀምሩ መግለፃቸውን ከኢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዋልታ
