=> የትግራይ ካህናትና ሊቃውንት ከሸዋ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ትርክቶች ኣርነታቸውን ሳይቀዳጁ የነፃ ኣውጭነት ሚና ተላብሰው ሲተርኩ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ ውጤት ያስመዘግባሉ። የተሳሳተ ትርክት ያልሰከኑ ቃላትና ቅጥያዎች ሲታከልበት ደግሞ ምን ያህል እንደሚያስነውር ገምቱት። እስቲ የተወሰኑትን ባጭሩ እንመልከታቸው። በትግራይና ተጋሩ ስም ስለሚሰራጩ እና ስለሚረጩ ነው በኣማርኛ ለመፃፍ የተገደድኩት።
1) ኣቡነ ተክለ ሃይማኖት የማእከላዊ ስልጣን ከኣገው የዛጉዌ ስርወ መንግስት በ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሰለሞናዊ ስረወ መንግስት ወደ ተባሉት (በ14ኛው ክፍለ ዘመን የትግራይ ካህናት ክብረ ነገስት ከዓረብኛ ወደ ግእዝ መተርጎም ተከትሎ) ነገስታት ማሻገር ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። የስልጣን ሽግግሩም በሃይልና በመሸናነፈ እንጂ እንደሚባለው በትርክትና በሽምግልና ኣይደለም። በውጤቱም ቤተ ክህነት ሲሶ የግብር መሬት እና የኣቃቤ ሰኣትና የእጨጌ ስልጣን በቤተ መንግስት ተሰጥቷታል። የሃይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሃላፊው ኣቃቤ ሰኣት: ኣቡነ ተክለ ሃይማኖት ደግሞ በእጨጌነት ኣሹማ የቤተ መንግስት ካቢኔ ኣባል ሆነች ማለት ነው። ነገር ግን ከትግራይ የሚነሱ መሰረተ ቢስ ወቀሳዎች መታረም ይኖርባቸዋል።
ሀ) ኣቡነ ተክለ ሃይማኖት የኣቡን ማእረጋቸው ትክክለኛ ነው። ብቸኛው ጦብያዊ ኣቡን ብለው ያስተማሩን ችግር ኣለባቸው እንጂ በዘመናቸው ሌላ ጦብያዊ (ትግራዋይ) ኣቡንም ነበሩ። ጦብያዊ ኣቡን እንዳይሾም ከግብፅ ጋር ተዋውለው ያቋረጡት ሰለሞናዊ ነገስታት ወደ ስልጣን ከወጡ ጀምሮ ነው። ፃድቁ ተክለ ሃይማኖት (ከእጨጌ ኣብነ ተክለ ሃይማኖት የቀደሙና የተለዩ ናቸው) ራሳቸው የኤጲስ ቆጶስ ማእረግ ይሰጡ እንደ ነበር ታሪካቸው ያወሳል።
ለ) ኣቡነ ተክለ ሃይማኖት የዛጉዌ ነገስታት የሰለሞን የትውልድ ሃረግ ስለሌላቸው ስልጣን ኣይገባቸውም ብለው የሰበኩበት ታሪክ የለም። ክብረ ነገስት ይዞት የመጣው ሰለሞናዊ ወራሾች ኣስተሳሰብ ጦብያ ውስጥ የተዘረጋው ንግስና ከኣገው ወደ ኣማራ ከተዛወረ በኋላ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ኣቡነ ተክለ ሃይማኖት ክብረ ነገስትን ትርክት ሳይደርሱበት ከዚህ ኣለም ተለይተው እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል።
ሐ) የኣቡነ (እጨጌ) ተክለ ሃይማኖት ገድል በፃድቁ ተክለ ሃይማኖት ገድል ላይ ደርበውና ጨማምረው የፃፉት ተከታዮቻቸው እንጂ ራሳቸው ኣቡነ (እጨጌ) ተክለ ሃይማኖት ኣይደሉም። መወቀስ ካለባቸው ተከታዮቻቸው እንጂ ኣቡነ ተክለ ሃይማኖት ኣይደሉም። በክብረ ነገስት ያለው ትርክት በገድሉ ላይ እንዲንፀባረቅ ያደረጉትም ተከታዮቻቸው ናቸው። በዚህም ሊወቀሱ ኣይገባም።
2) ደርግ የብሄር ጥያቄ ቅቡልነት ባገኘበትና የስታሊን ማርክሳዊ የብሄር ጥያቄ መፍቻ መንገድ በተሰራጨበት ነበር ወደ ስልጣን የውጣው። ደርግ በህብረ ብሄራዊነት እና ነባሩ ኣማራ ክርስትያን የኣገር ግንባታ ሂደት ማስቀጠል ላይ ኣጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ያመጣው መፍትሄ ብሄረሰቦች (ደርግ የመገንጠል ጥያቄ ለመዝጋት በጦብያ ብሄረሰብ እንጂ ብሄር የለም ብሎ ደምድሟል) እንደ ዳር ኣገር (periphery) ህዝቦች ቋንቋና ባህላቸው እንዲያንፀባርቁ ፈቀደ። መሰረተ ትምህርትም በኣካባቢ ቋንቋ ያስተምር ነበር። በሬድዮም የኣየር ሰኣት ተሰጥቷል። ኣማርኛ ቋንቋና የኣማራ ባህል ልእልና ለማስጠበቅ ደግሞ ኣማራ የሚባል ህዝብ ኣልነበረም። ኣማርኛ ቋንቋ በታሪካዊ ሂደትና መስተጋብር የጦብያ ህዝቦች በጋራ የፈጠሩት ነው የሚል ኣዲስ ትርክት ይዞ መጣ። ኣማርኛ ቋንቋ እና ኣማራዊ ባህል ተጫነብን ሳይባል mainstream ሆኖ እንዲቀጥል የተቀየሰ ዘዴ ነበር። ትርክቱ ጉልበት እንዳለው የሚያሳየው ደግሞ የትግራይ ካህናትና ሊቃውንት ተቀብለው እንደ በቀቀን ማስተጋባታቸው ኣንዱ ምስክር ነው። የትግራይ ካህናትና ሊቃውንት (የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች ጭምር) ከሸዋ እና ከደርግ ትርክት ባርነት ገና ኣርነታቸውን ኣላወጁም። የሸዋና የደርግ የትርክት ኣጥር ሆነው ወደ እነርሱ የተወረወረ ድንጋይ ነው እያነሱ የሚወረውሩት ። ባልሰከነ ስሜት ሲተረክ ደግሞ ያንገሸግሻል።
በ ተስፋኪሮስ ሳህለ
