የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን በማድረግ ለአገር ለውጥና እድገት እንዲሁም የስራ ዕድል ለመፍጠር በትጋት መስራት እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎትና ተግባራዊ የጥናትና ምርምር ውድድርና ኤግዚቢሽን ዛሬ በሲዳማ ክልል በሃዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ ተጀምሯል።
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን በማድረግ ለአገር ለውጥና እድገት እንዲሁም የስራ ዕድል ለመፍጠር በትጋት መስራት እንደሚገባ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለዚህ ያላቸው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ የተሟላ ክህሎትና እውቀት ያለው ዜጋ በማፍራትና ለሕዝቡ ጠቃሚ የሆኑ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለብልጽግና ጉዞ እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል።
በግብርናው መስክ ከራስ አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ በሚያስችል መልኩ ከክረምት በተጨማሪ በበጋ ማምረት መጀመሩንና ኮሌጆቹ ለዚህም ስራ አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል የስራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቴዎድሮስ ገቢባ እንዳሉት “ክህሎት ያለው ዜጋና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ኤግዚቢሽን እስከ ግንቦት አራት ይቆያል።
የጥናትና ምርምር ውድድርና ኤግዚቢሽን ከሲዳማ ክልል 11 የቴክኒክ ኮሌጆች በመምህራንና በተማሪዎች የተሰሩ 27 የፈጠራ ስራዎች ለውድድር እንደሚቀርቡ ኢዜአ ዘግቧል።
በውድድሩ የተሻለ ውጤት ላመጡ የገንዘብ የሜዳሊያና የሰርተፍኬት ሽልማት እንደሚሰጥ ገልጸው በውድድሩ በቀዳሚነት ያጠናቀቁ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
ዋልታ
