የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት ብዛት 13.5 ሚሊዮን መድረሱን የፓርቲው ፕሬዝዳንት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ፓርቲው ባለፉት ወራት በመቶ ሺህ አባላቱ ላይ “የማጥራት” እርምጃ መውሰዱን የገለጹት አብይ፤ ወደፊትም ተመሳሳይ አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ ጥቆማ ሰጥተዋል።
አብይ ይህን ያሉት ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ለሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ገለጻ ነው። አብይ ወቅታዊውን የፓርቲያቸውን አባላት ብዛት ጉዳይ የጠቀሱት፤ “የኢንተርፕሪዩነራል መንግስትን” የመፍጠር አስፈላጊነት ባስረዱበት የገለጻቸው ክፍል ላይ ነው።
ብልጽግና ፓርቲን “በአፍሪካ ትልቁ” ሲሉ የጠሩት የፓርቲው ፕሬዝዳንት፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲው 13.5 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት በገለጻቸው አስታውቀዋል። ብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጋቢት 2014 ባካሄደበት ወቅት፤ ፓርቲው ያሉት አባላት ብዛት 11 ሚሊዮን እንደሆነ አብይ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ጠቅሰው ነበር። የአብይ የአሁኑ ገለጻ፤ 2.5 ሚሊዮን አዳዲስ አባላት ባለፈው አንድ ዓመት ገደማ ጊዜ ውስጥ ገዢውን ፓርቲ መቀላቀላቸውን ያመለከተ ሆኗል።
