Cyber Power Tigray Media (CPT media )

ሳይበር ፖወር ትግራይ ሚድያ – ነፃን ህዝባውን ሚድያ እዩ!


Follow us on:
አማርኛ ዜና
0

የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት ለፖሊስ አቅም መጠናከር የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተጠቆመ

መደበኛ ፖሊስን የተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም ለፖሊስ አቅም መጠናከር የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ገለጹ።

የክልሉ የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላትን በተለያዩ የጸጥታ ዘርፎች መልሶ ለማደራጀት በተወሰደው እርምጃ የመደበኛ ፖሊስን የመረጡትን “ወንጀልን የመከላከል የመደበኛ ፖሊስ” ስልጠና በመውሰድ በዛሬው እለት ተመርቀዋል።

የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ እንዳስታወሱት በክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች ማካተት ያስፈለገው ጠንካራ አገራዊ የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት ነው።

የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላትንም እንደየምርጫቸው በመደበኛ፣ በማረሚያ ቤት፣ በአድማ ብተናና በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በመከላከያ ሰራዊት በማካተት የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ወጥነት ያለውና ጠንካራ የጸጥታ መዋቅር መገንባት በማስፈለጉ መሆኑን አስረድተዋል።

ጠንካራ የጸጥታ አካል እንዳይኖር የሚፈልጉ ኃይሎች የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማናፈስና ውዥንብር በመፍጠር ልዩ ኃይሉን ለመበተን ያሴሩት ሴራ ከሽፏል ብለዋል።

የወንጀል መከላከል ስልጠና ወስደው የመደበኛ ፖሊስን የተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላትም ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም ለክልሉ ፖሊስ አቅም መጠናከር የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ በበኩላቸው ስልጠና የወሰዱ የዛሬ ተመራቂዎች የሚሰጣቸውን ፖሊሳዊ ተልእኮ በመወጣት ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ፖሊስን መቀላቀላቸው ለክልሉ መደበኛ ፖሊስ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

አባላቱ በስልጠናው ያገኙትን ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ሰላምን በማስፈንና መረጋጋትን በመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች የሚያሰራጩትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ወደ ጎን በመተው ፖሊሳዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

እንደኢዜአ ዘገባ በምረቃ ስነ ሥርአቱ ላይ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልና የዞን አካላት መሳተፋቸው ታውቋል።

ዋልታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *