የሱዳን ጦር የተኩስ አቁም እና የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር እያደረገ የነበረውን ውይይት በዛሬው ዕለት መቋረጡን የሱዳን ዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልጸዋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ፣ ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው ግጭት በቆዳ ስፋት በአፍሪካ ሶስተኛ የሆነችውን ትልቅ ሀገር ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ስጋት ፈጥሯል።
በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በሁለቱ ኃይሎች መካከል በተደረገው ድርድር ሲቪሎችን ለመጠበቅ እና የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ለማድረግ ቢስማሙም ስምምነቶቹ በተደጋጋሚ ተጥሰዋል።
የሱዳን ጦር በጄዳህ ከሚደረገው ድርድር መውጣቱን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ቃል አቀባይ ሞሃመድ ኤል ሃሰን ሌባት እንደተናገሩት፣ “ይህ የሚያስገርም አይደለም ብዙ ጊዜ ይከሰታል። አስታራቂው አካል ሁለቱንም ወገኖች ወደ ስምምነት ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት ይሳካል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
በዚህ ጊዜ ግጭቱ በሁለቱ የአባይ ወንዞች መገናኛ እና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያ በሆነችው ካርቱም አቅራቢያ እየተደረገ ይገኛል።
በመዲናዋ ካርቱም ከፍተኛ ዘረፋ እንዲሁም የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት መቆራረጥ የተስተዋለ ሲሆን አብዛኞቹ ሆስፒታሎችም ሥራ አቁመዋል።
