አሲዳማ አፈርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከም በሚያስችል ሁኔታ ላይ የማዕድን እና የግብርና ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ የዜጎችን የምግብ ፍላጎት ለማረጋገጥ አሲዳማ አፈርን ማከም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በግብርና ኖራ አመራረት ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ማዕድን ሚኒስቴር ምርትና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለውን አሲዳማ አፈር ከሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ጋር በጋራ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው ሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
የሚኒስቴሮቹ የስራ ኃላፊዎችም በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን አሲዳማ አፈር በኖራ ድንጋይ ለማከም የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅርው ስራ ጀምረዋል፡፡
አሲዳማ አፈር በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምርትና ምርታማነት በአንዳንድ አካባቢዎች እየቀነሰ መምጣጡ ተገልጿል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በደቡብ ክልሎች የአሲዳማ አፈር ተጠቂዎች መሆናቸው ከማዕድን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይም በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄከታር መሬት በከፍተኛ ሁኔታ በአሲዳማ አፈር ተጠቅቷል ነው የተባለው፡፡
ዋልታ
