የመንግስት ባለስልጣናት በውጭ ሀገራት የሚያደርጉት ህክምና ከአሁን በኋላ “እንደማይፈቀድ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናገሩ
መንግስት የስራ ኃላፊዎች ለህክምና ወደ ውጭ ሀገራት የሚያደርጉት ጉዞ ከአሁን በኋላ “እንደማይፈቀድ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። የስራ ኃላፊዎቹ በውጭ ሀገራት ያሏቸውን የህክምና ቀጠሮዎች ከዛሬ ጀምሮ በመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲያካሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዝዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ በቢሾፍቱ ከተማ የተገነባውን የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 10፤ 2016 በመረቁበት ወቅት ባሰሙት ንግግር ነው። መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠለተ ከ35 ዓመት በኋላ መመረቁ የተነገረለት ይህ ሆስፒታል፤ የኩላሊት እጥበት፣ የነርቭ፣ የሳምባ እና መተንፈሻ አካላትን ጨምሮ ሌሎችንም የህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የምረቃ ንግግራቸው፤ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ለግንባታ በፈጀው ጊዜ እና በዘመናዊነቱ “ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሆስፒታሎች ይለያል” ብለዋል። “በዚህ ጥራት፣ በዚህ ስፋት፣ በዚህ የቴክኖሎጂ አቅም የተሰራ ሆስፒታል ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሌለ፤ በሀገራችን ደረጃ አሁን ባለው ሁኔታ አንደኛው ሆስፒታል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል” ሲሉም አብይ ተናግረዋል።
አብይ “ድንቅ ሆኖ የተሰራ” ሲሉ የጠሩትን ይህን ሆስፒታል፤ በውጭ ሀገራት የህክምና ክትትል የሚያደርጉ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ሊገለገሉበት እንደሚገባ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። “ከእንግዲህ በኋላ ወደተለያዩ ሀገራት ለህክምና የሚሄዱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፤ የህክምና ቦታቸው ቢሾፍቱ መሆኑን ከዛሬ ጀምሮ እንዲያውቁ አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።
Ethiopia Insider
