በሶማሌ ክልል ለ2016 የትምህርት ዘመን የሚሰራጭ ተጨማሪ ከ900 ሺህ በላይ መጽሐፍት ሕትመት እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አብዱላሂ አብዲ አደን በክልሉ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበጀት አመቱ በየትምህርት አይነቶቹ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከ467 ሺህ በላይ የመማሪያ መጽሐፍት ታትሞ መሰራጨቱን ገልጸዋል።
ለመጪው 2016 ትምህርት ዘመን ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚሰራጭ ተጨማሪ ከ900 ሺህ በላይ የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት ህትመት ከወዲሁ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በመደበው 200 ሚሊየን ብር የመጽሐፍት ሕትመቱ እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የመጸሐፍት ሕትመቱ እየተካሄደ ያለው ዘንድሮ የታየውን እጥረት በመፍታት በቀጣዩ ትምህርት ዘመን በየትምህርት አይነቶቹ ለሁለት ተማሪዎች አንድ መጽሐፍ ለማዳረስ ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በጅግጅጋ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል የዊልዊል 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሰሀል መሀመድ በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቤቱ ከ6ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው በአዲሱ ስርአተ ትምህርት የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል።
እጥረቱን በጊዜያዊነት ለማቃለል በፎቶ ኮፒ በማባዛት ለተማሪዎች እንዲከፋፈል መደረጉን ጠቁመው ለ2016 ትምህርት ዘመን ከወዲሁ የመጽሐፍት ሕትመት መጀመሩ ተስፋ ሰጭ መሆኑን አመልክተዋል።
ዋልታ
