የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዊንዶው ኦፍ አፍሪካ ፓርክ ግንባታ ስራን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል፡፡
የዊንዶው ኦፍ አፍሪካ ፓርክ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ ቀደም ብሎ ለፓርክነት ተከልሎ በነበረ ስፍራ ላይ የሚገነባ ሲሆን÷ አጠቃላይ 84 ሄክታር መሬት እንደሚሸፍን ተመላክቷል።
በፕሮጀክቱ የእያንዳንዱን የአፍሪካ ሀገር ባህል እና ማንነት የሚያንጸባርቁ ቅርሶች እንደሚቀመጡም ነው የተገለጸው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷በለውጡ ማግስት ከገባነው ቃል አንዱ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብና አዲስ እናረጋታለን የሚል ነበር፤ ያንንም በተግባር እያረጋገጥን ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ መዲና ወደ ሆነችው አዲስ አበባ አፍሪካውያን ሲመጡ ራሳቸውንና መልካቸውን የሚመለከቱበት ትልቅ ፕሮጀክት ነው ያስጀመርነው ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ በ14 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የመዝናኛ ፣ የመናፈሻ ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ ሰው ሰራሽ ሃይቅ እና መዋኛ ገንዳዎች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እንዲሁም የህጻናት መጫዎቻ ስፍራዎችን በውስጡ እንደሚይዝ ተጠቁሟል፡፡
ፋና
