ግንቦት 3/2015 (ዋልታ) “ኦሬንጅ” የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢ በዘርፉ በኢትዮጵያ የመሠማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ በቴሌኮም ዘርፍ ላይ የተሠማራውን የ“ኦሬንጅ” ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀሮም ሄኒክ በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በቴሌኮሙ ዘርፍ ከውጭ ባለሐብቶች ጋር ለመሥራት ያሳየውን ቁርጠኝነት ጠቅሰው በጋራ ለመሥራት በሚቻልባቸው ገዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ በቴሌኮሙኒኬሽኑ ዘርፍ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኦሬንጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀሮም ሄኒክ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በአፍሪካ የቴሌኮም ገበያ ውስጥ መዋዕለ-ንዋዩን አፍስሶ ያስመዘገበው ስኬት አብራርተዋል።
በቀጣይም “ኦሬንጅ” በዘርፉ ሥራዎቹን ዕውን ለማድረግ በሚችልባቸው ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዋልታ
