ኢትዮጵያ ጣምራ ሰብሳቢ በነበረችበት የመጀመሪያው የ2011 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ስደተኞች መድረክ ላይ በተገቡ ቃልኪዳኖች መሰረት ውጤታማ አፈፃፀም ማሳየቷ ተገለፀ፡፡
የ2011 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ስደተኞች መድረክ በተገቡ ቃልኪዳኖች አፈፃፀምና በቀጣይ በጄኔቭ ለሚካሄደው አለምአቀፍ የስደተኞች መድረክ ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በዕለቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የ2011 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ስደተኞች መድረክ ላይ በተገቡ ቃልኪዳኖች መሰረት ውጤታማ አፈፃፀም አሳይታለች ብለዋል፡፡
ለዚህም በጉባኤው በተገቡ ስምምነቶች መሰረት ስደተኞችን በመቀበልና የኑሮ ሁኔታቸውን የተሻለ ለማድረግ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በትምህርት ተደራሽነት፣ በማህበራዊ ጥበቃ እንዲሁም በሀይል አቅርቦት ዙሪያ በርካታ ስራዎች መስራቷን ነው የገለፁት።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሁለተኛ ያስባላትን 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኞችን አስጠልላ እንደምትገኝ ያብራሩ ሲሆን ስደተኞቹም በዋናነት ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ በጄኔቭ ለሚካሄደው አለምአቀፍ የስደተኞች መድረክ ላይ እየመከረ የሚገኘው ጉባኤው፤ ኢትዮጵያ ቅድመ ዝግጅቷን የምታመላክትበትም ጭምር እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በጉባኤው ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት የስራ ሀላፊዎች፣ የለጋሽ ሀገራት ተወካዮች እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዋልታ
