ኢትዮጵያ በዲጂታል ፖሊሲዎቿ ለሴቶች ትኩረት መስጠቷን ዓለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ሕብረት አስታወቀ።
ሕብረቱ ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሏት ደንቦችና ፖሊሲዎች ውስጥ የሴቶችን ተካትቶ በሚመለከት ያስጠናውን የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል።
በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ በቅርቡ ባወጣቻቸው የዲጂታል ፖሊሲዎቿ ውስጥ ለሴቶች የተለየ ትኩረት መስጠቷን ሕብረቱ ገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ሁሪያ አሊ ጥናቱ የኢትዮጵያን የዲጂታል ክፍፍል በማሳየት በዲጂታል ስነ-ምህዳር ውስጥ ለስርዓተ ጾታ ማካተት ምላሽ የሚሰጡ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት ያግዛል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዲጂታል ስነ-ምህዳር ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሕብረት የቴሌኮሚዩኒኬሽን ልማት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ኮስማስ ዛቫ ዛቫ (ዶ/ር) ጥናቱ የሴቶችን የዲጂታል ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያግዙ ምክረ ሃሳቦችን ያስቀመጠና በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮች አቅጣጫዎችን የሚጠቁም መሆኑን አመልክተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጾታ፣በእድሜ፣በአካባቢ፣በዲጂታል ክህሎትና በሌሎችም መስኮች የሚታይ የዲጂታል ክፍፍልን ለመቅረፍ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዋልታ
