ኢትዮጵያ በወንጀል ጉዳዮች ላይ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እንዲሁም ከቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችላት የትብብር ስምምነት አዋጅ ጸድቋል፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 19ኛ መደበኛ ጉባዔ ተካሂዷል፡፡
በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በቱርክ መንግስት መካከል የተደረገውን የወንጀል ጉዳዮች የጋራ ሕግ ትብብር ስምምነት፤ እንዲሁም ከሁለቱ መንግሥታት ጋር የተደረገውን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ለማጽደቅ በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የቀረቡት የስምምነት ረቂቅ አዋጆች ሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሚኖራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር፣ የሀገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የመንግስትን ስራ ለማሳለጥ እንደሚያግዝ የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክር ቤቱ አራቱም ረቂቅ አዋጆች ላይ በቅደም ተከተል ድምጽ የሰጠ ሲሆን÷በሶስት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ አዋጅ ቁጥር 1290/2015፣ 1291/2015፣ 1292/2015 እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1293/2015 ሆነው በአብላጫ ድምጽ ጸድቀዋል፡፡
FBC
