ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ በፖለቲካ ምክክር እና በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
አገራቶቹ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ የገቡትን የኮሎምቢያ ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዝዳንት ፍራንሲያ ኢሌናን ዛሬ ምሽት በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅትም ኮሎምቢያ ከ50 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ዳግም ለመክፈት በመወሰኗ የተሰማቸውን አድናቆት ገልፀውላቸዋል።
አቶ ደመቀ፣ ሁለቱ አገራት በአለም አቀፍ መድረኮች ተመሳሳይ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ያስታወሱ ሲሆን ኢትዮጵያ በቀጣይ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም፣ በአቪዬሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ከኮሎምቢያ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላት ለምክትል ፕሬዝዳንቷ ገልፀውላቸዋል።
ኮሎምቢያ በቀጣይ ዓመታት በተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተዘዋዋሪ አባል ቦታ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቧን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጠናዊ እና ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ይበልጥ በትብብር እንዲሰሩ ያግዛል ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቷ ኮሎምቢያ ዳግም በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ለመክፈቷ አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በቀጠናው ያላት ጠንካራ ተፅዕኖ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን፣ ውሳኔውም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ኮሎምቢያ በቀጠናዊና አህጉራዊ እንዲሁም በባለብዙ መድረኮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
ኮሎምቢያ በአለም መድረክ የምትታወቅበትን የቡና ልማት ቴክኖሎጂ መልካም ተሞክሮ ለኢትዮጵያ እንደምታጋራም መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያና ኮሎምቢያ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1947 ሲሆን አገሪቱ በ1967 በአዲስ አበባ የከፈተችውን ኤምባሲ እ.አ.አ በ1974 መዝጋቷ አይዘነጋም።
ኢዜኣ
