
23 ሰኔ 2024, 10:49 EAT
የኢትዮጵያ ወታደሮች እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የሆነውን አል-ሸባብን እያሳደዱ ከሶማሊያ መንግሥት ፍቃድ ውጪ የሶማሊያን ድንበር አቋርጠው ገብተው እንደነበር ተነገረ።
ከኢትዮጵያ ጋር ከሚካለሉ የሶማሊያ ግዛቶች መካከል አንዷ የሆነችው የሂራን ግዛት ከተማ ማታባ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላትን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የማታባን ከተማ አስተዳዳሪ ወታደሮቹ የአል-ሸባብ ታጣቂዎችን እየተከተሉ ከመንግሥት ፍቃድ ውጪ የሶማሊያን ድንበር ማቋረጣቸውን ከገለጹ በኋላ የሠራዊቱ አባላት ወደመጡበት መመለሳቸውን በ ሶማልኛ ተናግረዋል።
በደቡባዊ ሶማሊያ የምትገኘው ሂራን ግዛት አስተዳዳሪ በሽር አብዲራሃማን ሼኬዬ በ ሶማልኛ ሲናገሩ፤ ወደ ሶማሊያ ግዛት ገብተው የነበሩት ወታደሮች ቁጥር ወደ 3ሺህ እንደሚጠጋ ገልጸዋል።
አንዳንዶች በቁጥር ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ የሚያደርሷቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከኢትዮጵያዋ ፈርፈር ከተባለች የድንበር ከተማ ተነስተው ሶማሊያ የገቡት አርብ ሰኔ 14/2016 ዓ.ም. መሆኑ ተነግሯል።
በሽር አብዲራሃማን ሼኬዬ ከኢትዮጵያ ወታደሮች፣ ከግዛቷ አስተዳዳሪዎች እና ከሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ጋር ንግግር ከተደረገ በኋላ የሠራዊት አባላቱ ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጉን አመልክተዋል።
ይህንን የኢትዮጵያ ወታደሮች ስምሪትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
- የእስራኤል ወታደሮች የቆሰለን ፍልስጤማዊ ተሸከርካሪ ላይ አስረው መውሰዳቸው ቁጣን ቀሰቀሰ23 ሰኔ 2024
- ሩሲያ በዩክሬን የኃይል ማመንጫዎች ላይ ‘ከባድ’ ጥቃቶችን ሰነዘረች23 ሰኔ 2024
- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ አዲስ መንግሥት ለመመሥረት ምርጫ እየተካሄደ ነው23 ሰኔ 2024
ሂራን ኦንላይን የተባለ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው ከሆነ የኢትዮጵያ ሠራዊት በፈርፈር የድንበር ከተማ አቅራቢያ የታዩ የአል-ሸባብ ተዋጊዎችን እያሰደዱ 70 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ሶማሊያ ድንበር ዘልቀው ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እውቅና ውጪ የሶማሊያ ድንበር ጥሶ ሲገባ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ሂራን እና ባኮል ወደ ተባሉ የሶማሊያ የድንበር አካባቢዎች ዘልቀው ገብተው ነበር።
ከሶማሊያ ባሻገር አል ሻባብ ዒላማ ሊያደርጋቸው ከሚፈልጋቸው የአካባቢው አገራት ኢትዮጵያ ዋነኛዋ ስትሆን፣ ቡድኑ በተደጋጋሚ ያደረጋቸው የጥቃት ሙከራዎች በኢትዮጵያ የደኅንነት እና የመከላከያ ኃይሎች መክሸፋቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመትም አልሻባብ በሶማሌ ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ ተዋጊዎቹን አስርጎ ለማስገባት ባደርገው ሙከራ በርካታ አባላቱ እና አዛዦቹ መገደላቸው አይዘነጋም።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር እና ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በተደረሰ ስምምነት ኢትዮጵያ ወደ አስር ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች በሶማሊያ ውስጥ ያላት ሲሆን፣ በቅርቡ በሁለቱ አገራት መካከል በተከሰተ አለመግባባት ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር ከግዛቷ እንዲወጣ ጠይቃለች።
ይህ የአሁኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ዘልቆ መግባት የተከሰተውም የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተበላሸበት እና የሶማሊያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ተከትሎ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን እየከሰሱ ባለበት ወቅት ነው።
