ቻይና በአገሯ ውስጥ ያመረተችው የመጀመሪያው የመንገደኞች ጄት አውሮፕላን ተሳፋሪዎችን ይዞ የመጀመሪያውን የተሳካ የንግድ በረራ አደረገ።
የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ሲ919 የተባለው አውሮፕላን ተሳፋሪዎችን ይዞ ዛሬ እሁድ ጠዋት ከሻንግሃይ በመነሣት ወደ ዋና ከተማዋ ቤይጂንግ ሲያመራ አሳይቷል።
ይህ የቻይና የመጀመሪያው የመንገደኞች አውሮፕላን ኮሜርሺያል አቪዬሽን ኮርፖሬሽን ኦፍ ቻይና (ኮማክ) በተባለው ድርጅት የተሠራ ሲሆን፣ በኤርባስ እና በቦይንግ ጄቶች በበላይነት የተያዘውን የአውሮፕላን ምርት ዘርፍ ሰብሮ ለመግባት አገሪቱ ያያዘችው ዕቅድ ነው።
ነገር ግን ይህ 164 መቀመጫዎች ያሉት በቻይና የተሠራው አውሮፕላን ሞተሩን ጨምሮ አብዛኛውን ወሳኝ ክፍሎቹን የሚያገኘው በምዕራብ አገራት ውስጥ ከሚገኙ የአየር በረራ ቴክኖሎጂ አምራቾች ነው።
የመጀመሪያው አውሮፕላን ከ130 በላይ መንገደኞችን በማሳፈር ከሻንግሃይ ወደ ቤይጂንግ ያደረገውን ቀዳሚ የንግድ በረራውን ከሦስት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ችሏል።
አውሮፕላኑ በተጨማሪም ከቤይጂንግ ወደ ተነሣባት የባሕር ዳርቻ ከተማዋ ሻንግሃይ የመልስ ጉዞ እንደሚያደርግም ፕሮግራም ተይዞለታል።
የቻይና መንግሥት ንብረት የሆነው ቻይና ኢስተርን አየር መንገድ፣ አምስት ተመሳሳይ አውሮፕላኖች እንዲመረቱለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አውሮፕላኑን ያመረተው ኮማክ የተባለው ተቋም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ 150 አውሮፕላኖችን ለማምረት ዕቅድ ይዟል።
ጨምሮ እንደገለጸውም አስካሁን 1 ሺህ 200 ሲ919 የተባሉትን የመንገደኞች አውሮፕላኖችን እንዲያመርት ከተለያዩ አየር መንገዶች ትዕዛዝ ተቀብሏል።
አንዳንድ የአየር ትራንስፖርት ባለሙያዎች እንዳሉት ግን ይህ ከተጠቀሱት የአውሮፕላን ምርት ትዕዛዞች ውስጥ አብዛኞቹ ከአገር ውስጥ አየር መንገዶች የቀረቡ የፍላጎት መግለጫዎች እንጂ የቀጥታ ትዕዛዞች ላይሆኑ ይችላሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ከጥቂት ዓመት በፊት የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ለማሳያነት በተዘጋጀው የሲ919 አውሮፕላን ሞዴል የአብራሪዎች ክፍል ውስጥ ተቀምጠው አውሮፕላን የማምረቱን ፕሮጀክት “የቻይና ፈጠራ የተሞላበት አንዱ ስኬት ነው” ብለው ገልጸውት ነበር።
ኢዜኣ
