ትዊተር ኩባንያ ከጽሑፍ እና ፎቶ በተጨማሪ የድምፅ እና ቪድዮ ጥሪ ማድረግ የሚያስችል አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡
የትዊተር ባለቤት ኤለን መስክ በትዊተር ገጹ እንዳስታወቀው “በቅርቡ ከማንኛውም ሰው ጋር በትዊተር አድራሻ የድምጽ እና ቪዲዮ መልዕክት መለዋወጥ የሚያስችል አገልግሎት በዚህ መድረክ ላይ እየመጣ ነው” ብሏል፡፡
አገልግሎቱ ሲጀመር ማንኛውም ሰው በየትኛውም ዓለም ከሚኖር ሰው ጋር ስልክ ቁጥሩን መስጠት ሳይጠበቅበት መነጋገር ይችላልም ነው የተባለው፡፡
በዚህም ትዊተር በሜታ ኩባንያ ባለቤትነት እንደተያዙት ዋትስአፕ፣ ሜሴንጀር እና ኢኒስታግራም የድምፅ፣ ጽሑፍ፣ ፎቶ እና ቪዲዮ መልዕክቶችን መለዋወጥ የሚያስችል አገልግሎት መስጠት ያስችለዋል፤ ልምድ ካካበቱት ከሜታ መተግበሪያዎች ጋርም ለመወዳደር ያስችለዋል ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መልዕክቶች እንዳይጠለፉ ከላኪ እስከ ተቀባይ የማመስጠር (end-to-end encryption) አገልግሎትም መስጠት እንደሚጀምር ባለቤቱ ኤለን መስክ በመልዕክቱ አስታውቋል፡፡
ዋልታ
