ባለፉት 9 ወራት ከግብርናው ዘርፍ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር የ2015 የ9 ወራት ግምገማ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ነው።
በ2014/15 የመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው መሬት 482 ሚሊዮን ኩንታል መገኘቱን የገለጹት የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ በ2015 በበጋ መስኖ 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በበጋ የስንዴ መስኖ ተሸፍኗል ብለዋል።
በ2015 ስንዴ ወደ ውጭ መላክን ጨምሮ በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ውጤታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በዘጠኝ ወራቱ በግብርናው ዘርፍ ላይ ለ943 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯልም ነው የተባለው።
በበጋ መስኖ የለማውን የስንዴ ሰብል በዝናብ ሳይበላሽ ማሰባሰብ፣ በበልግ እና በቀጣይ የልማት ሥራዎችን ማሳለጥ፣ የእንሰሳት እና የመኖ ልማት፣ እንዲሁም የ2015 የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ ትኩረት የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።


ምንጭ፡ ኢዜኣ
