በፍትሕ ዘርፉ ፈጣን፣ ተጨባጭ እና እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት የሕግ ፍኖተ-ካርታው በአስቸኳይ ሊተገበር እንደሚገባ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ መድረክ ላይ የሕግ ፍኖተ-ካርታውን በመተግበር ዕቅዱን ለማሳካት ተቋማት ተገንብተው የሕግ የበላይነት የተከበረባት ሀገር ለመፍጠር በትብብር ተግተን ልንሠራ ይገባል ሲሉም አፌ- ጉባኤው አሳስበዋል።
ከለውጡ ወዲህ ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ሕጎች ተሻሽለው አመርቂ ውጤቶች መታየተቸውን አስታውሰው፣ ሀገር አቀፍ የማሻሻያ ሕጉ ሲተገበር የተጠያቂነት ሥርዓት እንደሚፈጠር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል እና ዜጎችን የፍትሕ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።
አፈ-ጉባኤው የሕግ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታው ዝግጅት እና አተገባበር አስከ ሰኔ ወር መጨረሻ 2015 ዓ.ም ድረስ መጠናቀቅ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በፍኖተ-ካርታው መሠረት የሕግ ማሻሻያውን የአፈጻጸም ሂደት መከታተል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፣ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት የፍትሕ ዘርፉ ነፃ እና ገለልተኛ እንዲሆን የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን እንደነበር አስታውሰው፣ የሕግ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታው በፍጥነት መተግበር እንዳለበት የምክር ቤት አባላት በውክልና ሥራቸው ወቅት ሕዝቡ ያነሳላቸው ዋና አንገብጋቢ ጥያቄ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሀገር አቀፍ የሕግ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታው የትግበራ ሥራው ሲጀመር ሕዝቡን ያሳተፈ፣ በባለድርሻ አካላት የታወቀ እና ሥራው የተፋጠነ እንዲሆን የክንውን ተግባራቱን ምክር ቤቶች ኃላፊነት ወስደው በበላይነት ሊመሩት እንደሚገባ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ምንም እንኳ ሦስቱም የመንግሥት አካላት የየራሳቸው ተግባር እና ተልዕኮ ቢኖራቸውም የሕግ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታው ለሀገሪቱ ሰላም እና ዕድገት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የላቀ አስተዋፅኦ ስላለው በትብብር መሥራት እንዳለባቸው እና ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት አስታውቀዋል።
የሚቀጥለው ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ በሐረሪ ክልል የሚካሄድ እንደሆነ አቅጣጫ መቀመጡን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ መድረክ ከሕንድ ፓርላማ ሉግሳቫ የተገኙ የልምድ ተሞክሮዎች ሰነድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከሕንድ ፓርላማ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ለሁለቱም ምክር ቤቶች የሚጠቅሙ እና ወደ ተግባር ወርደው ቢሠራባቸው የተሻለ ውጤት የሚያስገኙ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ዋልታ
