የትግራይ ህዝብ የምን ጊዜም ምርጫ ሰላም ነው። ከፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ ለስምምነቱ በተሟላ መልኩ መፈፀም ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀራረብ የህዝባችን ስቃይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል። ከስምምነቱ በተሟላ መልኩ መረጋገጥ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል በሚገኙ ወገኖች በኩል ይነሱ የነበሩ ከሕግም ከአመክንዮም ጋር ያልተያያዙ ጥያቄዎችን ሰከን ባለ መንገድ ለመፍታት በፌዴራል መንግስቱ ይደረጉ የነበሩ ጥረቶችን ለማገዝ የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይሁንና የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይደረግ የነበረው ዳተኝነት በስተመጨረሻ በክልሉ የሚገኙ ፅንፈኞችና አጋሮቻቸው ትግራይ ላይ አሰበዉት የነበረውን የጥፋት አላማ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዳከሸፈባቸው በአደባባይ የሚያማረሩበት፣ ብሎም ከፌዴራል መንግስት ጋር ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ሲፈጠርም ፀረ ፕሪቶሪያና ፀረ ትግራይ አቋማቸውን በግልፅ በማራገብ ላይ ይገኛሉ። ይህንን እንቅስቃሴ እንመራለን የሚሉት አመራሮችም ሆኑ አጋሮቻቸው እንዲሁም ያሰማሯቸው የሚድያ አፈቀላጤዎችና የርእዮተ አለም መሪዎች ፣ መከላከያ ሰራዊቱ በመውሰድ ላይ ያለውን እርምጃ ‘የህወሓት ቀጥተኛ ተሳትፎ አለበት’ በሚል በሬ ወለደ ጩኸት እየደረሰባቸው ላለው ሽንፈት የትግራይን ህዝብ ሰበብ ለማድረግ ሲዳክሩ ይሰማሉ። የፌዴራል መንግስት በነዚህ ሀይሎች ላይ እየወሰዳቸው ላሉ እርምጃዎች የትግራይም ሆነ የሌላ ወገን የተለየ ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለን አናምንም። ይሁንና ፀረ ሰላም አቋማቸውን ለማራመድ እስኳሁን ሲረጩት የነበረውን መርዝ አልበቃ ብሎ የትግራይን ህዝብ በትልቁ በትንሹ መወንጀል ቋሚ ስራ አድርገውት ይገኛሉ። ይህ ዘመቻ ፍፁም አሸናፊ ሊሆን የማይችል፣ የፅንፈኝነትና የፀረ ሰላም መንገድን ለማረም አያግዝም ብቻ ሳይሆን በህዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን ሰላማዊ ግንኙነት በእጅጉ የሚጎዳ ነው።
አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ሁሉም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያለው ቁርጠኛ አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማፍረስ የሚቋምጡ ፅንፈኛ ሀይሎችና የቅርብም የሩቅም አጋሮቻቸውን በህዝባችን ላይ የሚያደርጉትን ዘመቻ ለማክሸፍ ከፌዴራል መንግስት እስካሁን ድረስ እያደረግነው የመጣነውን አበረታች ግንኙነት አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር አቋሙን ግልፅ ማድረግ ይፈልጋል።
የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር
07 ነሐሰ 2015 ዓ/ም

