በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ዓመት በድርቅ ለተጎዱ 10 ዞኖች ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነትና የተለያዩ ድጋፎች መደረጉን የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ገለጸ።
ድጋፉ ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከክልሉ ህዝብ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የተገኘ መሆኑም ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል የቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ ሀብታሙ ሲሳይ እንደገለጹት የኦሮሞ ህዝብ የመደጋገፍ፣ መተጋገዝና የመረዳዳት ባህል የሆነው ቡሳ ጎኖፋ ስርዓት ተቋማዊ እንዲሆን ተደርጎ እሴቱን ለማጎልበት ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
የክልሉ መንግስት ቡሳ ጎኖፋን በአዋጅ በማቋቋም ህዝቡ ወደ ነበረበት የገዳ ስርዓት እሴት እንዲመለስ ማስቻሉን የገለፁት ኃላፊው በዚህም በዘንድሮው ዓመት በ10 የክልሉ ዞኖች የተከሰተውን ድርቅ በራስ አቅም ለመቋቋም ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተለይም በቦረና፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ባሌ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ድርቁ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል የተሻለ አቅም የተገነባበት ዓመት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በድርቁ በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችም በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ቡሳ ጎኖፋ የማይተካ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የተማሪዎች ምገባ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሀብት በጥሬ ገንዘብና በአይነት መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው እስከ መጪው ሰኔ ድረስ የሀብት አሰባሰቡን 3 ቢሊዮን ብር ለማድረስ በዘመቻ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በዚህም በመጪው ዓመት በሁሉም ትምህርት ቤቶች የምገባ መረሐ ግብር ለማስኬድ መታቀዱን ገልጸው ሀብት የማሰባሰቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመጨረሻም ተተኪው ትውልድ ባህሉን እንዲያውቅና እንዲያጎለብት ለማስቻል ጭምር እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው ይህም ቡሳ ጎኖፋን የመሳሰሉ ባህላዊ የመደጋገፍ እሴቶችን ለማጠናከር ግንባር ቀደም ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል።
ዋልታ
