በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ባጠናው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በሪፖርቱም ከታህሳስ 23/2014 እስከ ታህሳስ 23/2015 በፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ እና ቴሌግራም ላይ የተሰራጩ መረጃዎች ዳሰሳ መካተታቸው ተገልጿል።
በነዚህ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የተሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ለመመርመርም የተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች እና የግለሰቦች ገጾች ላይ ምልከታ መደረጉ ተወስቷል።
በዚህም ፓለቲካን፣ ብሄርን፣ ሃይማኖትን፣ የአካል ጉዳትን እና ፆታን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች የተሰራጩ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የጥላቻ ንግግሮቹ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር፣ ተቋማትን፣ ፖለቲካኞችን፣ የተለያዩ ቡድኖችን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዒላማ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡
በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የጥላቻ ንግግር የተስተዋለባቸው ሲሆን ፌስቡክ በዋነኝነት ብሄር ተኮር የጥላቻ ንግግር የተሰራጨበት ነበር ተብሏል። ዩቲዩብ እና ቲክቶክ ደግሞ ግለሰብ ላይ ያተኮሩ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃዎች ተስተውለውበታል።
ታሪክ እና ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ያሉ ጠርዝ የያዙ አመለካከቶች ለጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ምንጭ መሆናቸው በሪፖርቱ የተገለፅ ሲሆን ይህም የሀገር ሰላምን የሚያናጋ እና አብሮ የመኖር እሴትን የሚሸረሽር ሆኖ መገኘቱም ተመላክቷል።
በዋነኝነት ስድብ፣ ማጥላላት፣ ማንቋሸሽ፣ ማግለል፣ ለሁከት እና ብጥብጥ ቀስቃሽ የሆኑ ይዘት ያላቸው ሀሳቦች በፅሁፍ እና ቪዲዮዎች መሰራጨታቸውም ነው የተገለፀው።
አብዛኛዎቹ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የተገልጋዮችን ደህንነት ለመጠበቅ ህግና ደንብ ቢያስቀምጡም ተገቢውን እርምጃ አለመውሰዳቸውም ተጠቅሷል።
የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃን በሚመለከት ሪፖርት ካደረጉት መካከል 64 በመቶ ያህሉ መልዕክቱ በድርጅቱ የይዘት ተቆጣጣሪዎች እንዳልተነሳላቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ በተገቢው አለመተግበርም ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል ነው የተባለው።
አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ ፖሊሲዎች መቅረፅ፣ የማህበራዊ ገፆች ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር ማድረግ እና ሌሎችም በጥናቱ በምክረ ሀሳብነት ደረጃ ተሰንዝረዋል።
