የጤና ሚኒስቴርና የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የሕክምና ስፔሻላይዜሽንን ማጠናከር የሚያስችል የ5 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ።
የፕሮጀክቱን ስምምነት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሠረትም የአውሮፓ ኅብረት “ከስፓኒሽ እና ጣሊያን ኮኦፐሬሽን” ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ዘጠኝ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የስፔሻላይዜሽን ተማሪዎችን እና አስተማሪዎችን የሙያ ብቃት ለማሳደግ ይሠራሉ ተብሏል።
ፕሮጀክቱን ይፋ የማድረግ መርሐ-ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤናውን ዘርፍ የበለጠ ለማጠናከር ለሰው ኃይል ግንባታ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጀምሮ በየደረጃው ያለውን የሰው ኃይል ለማብቃት ከሥልጠና ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች በመደረግ ላይ ናቸው ብለዋል።
የስፔሻላይዜሽን ሕክምና ሥልጠናን ማስፋት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሊያ፤ በአሁኑ ጊዜም በ22 የትምህርት ተቋማት የስፔሻላይዜሽን ፕሮግራሞች በመሰጠት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
በዛሬው ዕለት የአውሮፓ ኅብረት ይፋ ያደረገው ፕሮጀክት በዘጠኝ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን አቅም ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ ስምምነት መሰረትም የአውሮፓ ኅብረት “ከስፓኒሽ እና ጣሊያን ኮኦፐሬሽን” ጋር በመተባበር በ5 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ሥልጠናዎችን የማስፋት፣ ቁልፍ የሆኑ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ጥራት ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
በሌላ መልኩ ከእነዚህ አገራት ባለሙያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማስመጣት የልምድ ልውውጥ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ ለሕክምና ዶክተሮች ሥልጠናን ጨምሮ የአቅም ግንባታ ሥራዎች የሚተገበሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ኢዜኣ
