በሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ባሳለፍነዉ አርብ በመኪና አደጋ ሕይወታቸዉ ማለፉ ተሰምቷል።
ኢትዮጵያዊያኑ ቅዳሜ ለሚካሄድዉ የሰርግ ስነስርዓት ቁሳቁሶችን ሸምተዉ ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱ አደጋዉ ማጋጠሙ ተዘግቧል። ኹለት የ 20 እና ኹለት የ 19 ዓመት ወጣቶች እንዲሁም አንድ የ 17 ዓመት ታዳጊ ወጣት በአደጋው ሕይወታቸዉን ማጣታቸዉን በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሰምቻለሁ ሲል ብስራት ራዲዮ ዘግቧል።
አደጋዉ ከሌላ መስመር በከፍተኛ ፍጥነት ከመጣ ተሽከርካሪ ጋር በተከሰተ ግጭት መፈጠሩ የተገለጸ ሲሆን፤ አሽከርካሪዉ አደጋዉን ካደረሰ በኋላ ከመኪናዉ በመዉጣት ሮጦ ለማምለጥ መሞከሩም ተነግሯል።
በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ጥቆማ መሰረት ግለሰቡን የሚኒያ ፖሊስ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር አዉለዉታል ተብሏል። በተደረገለት ምርመራም ግለሰቡ አልኮልና አደንዛዥ እፅ ተጠቅሞ ሲያሽከረክር እንደነበረ ተረጋግጧል።
በሚኒሶታ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሶማሌ ተወላጆች በከፍተኛ ሀዘን ዉስጥ መሆናቸዉ የተነገረ ሲሆን፤ ማህበረሰቡም ለተጎጂ ቤተሰቦች እስካሁን 300 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ማሰባሰቡ ተሰምቷል። ምንጭ ብስራት ራዲዮ
