የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በማህብራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሀፍ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢውች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል።
በመሰረቱ ብዙ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ይኖራሉ ያሉት ደመቀ መኮንን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊና የውይይት አግባብ ነው ብለዋል።
ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ
- የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ
- ያለንን የሚያሳጣ
- በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ ነው ሲሉም አስፍረዋል።
‘ሰላም ከሌለህ ሁሉን ታጣለህ’ የሚባለውን እውነታ ከልብ በማጤን በአስተውሎት መጓዝ በሚገባን ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
በየዘመኑ ብዙ ፈተናዎች እና ችግሮች ሲገጥሙ በጥበብ ተሻግረው ያሻገሩንን የአባቶቻችን ጥበብና አስተውሎት ማጥበቅ ይጠይቃል፡፡ የሀገር ሽማግሌ የጠፋበት፣ ታላቅ የሌለበት፣ መካሪ የሃይማኖት አባት የታጣበት ይመስል ሁላችንንም የሚያባላና የሚበላ አካሄድ ይስተዋላል ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም የዚህ መጨረሻ በግራም በቀኝም ከውጭም ከውስጥም ላሰፈሰፉ ኃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖ አቅም የሚያሳጣ፣ ክብራችንን የሚጎዳ፣ ተጋላጭነታችንን የሚያሰፋ በአጠቃላይ ሁሉንም የሚያሳጣ እንዳይሆን ያሰጋል ብለዋል።
ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው ያላረኩንና ሌሎች ችግሮችና ስሜቶች ይኖራሉ፡፡
ለእነዚህ ጉዳዮች ቆም ብለን በማሰብ በሰላሙ መንገድ ዘላቂ መፍተሄ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል። አክለውም ለዚህም የሁሉም ዋስትና የሆነውን ህግና ሥርዓት በተሟላ መልኩ ማክበርና ማስከበር ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
