ለትምህርት ዘርፉ ጥራት ከተለምዷዊ ስርዓት የተላቀቁ፣ መምህራንን የሚደግፉና የመማር ማስተማሩን ሂደት በብቃት ሊመሩ የሚችሉ አመራሮችን ማፍራት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
በእንግሊዝ መንግስት የሚደገፈው ኤዱኬሽን ትረስት ፈንድ (Education Trust Fund) የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ይፋ ባደረገው ጥናት፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚደግፉ አመራሮች ማፍራት ባለመቻሉ በዘርፉ ላይ ክፍተቶች መፈጠራቸውን አመልክቷል።
አሁን ድርጅቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለአንድ አመት የሚቆይ የተግባር ስልጠናን ለርዕሰ መምህራኖች መስጠት መጀመሩን የገለፀ ሲሆን በዚህም እስካሁን ከ1700 በላይ አመራርና መምህራኖችን ማሰልጠን መቻሉን ጠቁሟል።
በ2013 ዓ.ም ለሙከራ በጥቂት ትምህርት ቤቶች የተጀመረው ይህ ስልጠና እስካሁንም እየተሰጠ መቆየቱ ተመላክቷል፡፡ በዛሬው ዕለትም ላለፈው አንድ አመት የተግባር ላይ ስልጠናውን ሲከታተሉ ለነበሩ ሰልጣኞች በድርጅቱ እውቅና ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀው ይህ እንዲሆን ዘርፉ ከፖለቲካ ሊላቀቅ ይገባል ብለዋል።
ባለፈው ስርዓት በተለይም መምህራኑንና የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚመሩ አመራርን የፖለቲካ አባል እንዲሆኑ ሲደረግ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ደግሞ ለትምህርት ጥራቱ መውደቅ እንደ መንስኤ ይጠቀሳል ብለዋል፡፡
ስለዚህ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ከዚህ የተላቀቀ እና የአስተሳሰብ ለውጥ ሊመጣ እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በትምህርት ዘርፉ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የትምህርት ዘርፉ ከፖለቲካው እንዲላቀቅ ከማድረግም በተጨማሪ የትምህርት ጥራቱን ሊያግዙ የሚችሉ ፖሊሲዎችን በመቅረፅ ወደ ስራ መግባቱንም የትምህርት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ዋልታ
