በመጪው ክረምት ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በ5ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሰራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ከዚህ በፊት እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አጠናክሮ ማስቀጠል ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።
ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ነፃ ንግድ ቀጠናው የኮርፖሬሽኑን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት የማቅረብ ስራዎችን እንዲሰሩና እንደየአካባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ችግኞች እንዲተከሉ አቅጣጫዎችን መቀመጣቸውም ተገልጿል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለፉት 4 ዙሮች በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የጽድቀት መጠናቸውም ከ90 በመቶ በላይ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢዜኣ
