“በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የሚደረግ ዛቻ ሊቆም ይገባል” ሲሉ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች አሳሰቡ።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፅንፈኛ ኃይሎችን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በሰቆጣ ከተማ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
የሰቆጣ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ መላሽ ወርቃለም በሰላማዊ ስልፉ ባስተላለፉት መልእክት፣ አማራ ክልልን መሪ አልባ ለማድረግ የሚያሴሩ ፅንፈኛ ኃይሎች በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ መንግሥት በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ፅንፈኞች በክልሉ አመራሮች ላይ እያደረሱ ያሉትን መጠነ ሰፊ ጉዳት አንታገስም ሲሉም ገልጸዋል።
“ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢያችን በነበረው ጦርነት የደረሰብንን ግፍ እና መከራ የዋግ ኽምራ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቀዋል፤ የሰላምን ዋጋም እንዲሁ” ያሉት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ስቡህ ገበያው፣ አሁን ላይ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም በምንም መልኩ ሊቀለበስ አይገባም ነው ያሉት።
በሰላም እጦት ሁላችንም እየታመስን መኖር የለብንም ያሉት ዶክተር ስቡህ፣ የቃየል እና የአቤል ዓይነት ግድያ በአንድ ወንድማማቾች መካከል እየተፈፀመ ያለው አስነዋሪ ተግባር ሊቆም እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሕዝባችን የሰላምን ሁለንተናዊ ምንነት ስለሚረዳ በጦርነቱ ሀብቱን፣ ሕይወቱን እና የሥነ-ልቦና ችግር ተጎጂ ሆኖ ያለፈበትን መከራ በእርግብ አምሳል ተመስሎ በሰላማዊ ሰልፍ የጦርነትን አስከፊነት ለመግለጽ አደባባይ መውጣቱ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
ሰላማዊ ሰልፈኞቹ፥ እኛ የዋግ ኽምራ ነዋሪዎች በኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና በኢትዮጵያዊነት የምናምን እንጂ ለፅንፈኛ ኃይሎች የማንበረከክ መሆናችን እናሳውቃለን፤ የክልላችን ልማት በነውጠኛ ኃይልች አይቀለበሰም የሚሉ እና ሌሎች የተለያዩ መልእክቶች በማስተላለፍ ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ከአስተዳደሩ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።




ምንጭ፡ ኢዜኣ
