በሊዝ ለጨረታ ከቀረቡት 287 ቦታዎች በአጠቃላይ 12.2 ቢሊዮን ብር ማግኘት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የለማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ 297 ያክል ቦታዎች ለጨረታ የቀረቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 4 ቦታዎች ለጨረታ ብቁ እንዳልሆኑ በባለሙያዎች መለየታቸው እና ሌሎች 6 ቦታዎች ደሞ በቂ ተጫራች ሳያገኙ ቀርተዋል።
በድምሩ13 ሄክታር ገደማ ስፋት ባላቸው በቀሪዎቹ 287 ቦታዎች ላይ በቂ ተጫራቾች ተገኝተው አሸናፊዎች የተለዩ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ውል ማሰር እና ሌሎች ሂደቶች እንደተገባ ገልጸዋል።
በሊዝ ለጨረታ ከቀረቡት ቦታዎች 7.7 ቢሊዮን ብሩን ተጫራቾች ቦታውን እንደተረከቡ ክፍያ የሚፈጽሙበት ሲሆን ቀሪው 4.5 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ በሰጠው የሊዝ መክፈያ የ5 ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚከፈል ነው።
በተደረገው ቦታዎችን በሊዝ ጨረታ የማስተላለፍ ሂደት በአራዳ ክፍለ ከተማ 1 ካሬ በ414 ሺህ ብር በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠው ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ20 ሺህ ብር የተሸጠው መሆኑ ተነግሯል።
አቶ ሀብታሙ የጨረታ ሂደቱ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ግልጽነት የተስተዋለበት እና ተጫራቾች እያንዳንዱን ሂደት በአካል እንዲከታተሉ የተደረገበት እንደሆነም ገልጸዋል።
ነገር ግን በጨረታው ሂደት ላይ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዙ አሰራሮች ስህተቶች ተፈጥረው እንደነበር ጠቅሰው፤ በችግሮቹ ላይ ማስተካከያ መደረጉን ነው የተናገሩት።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ፤ ተጫራቾችም ምንም አይነት ቅሬታ ካላቸው መስሪያ ቤቱ ይህንን ለማስተናገድ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።
ላለፉት አምስት ዓመታት መሬትን በሊዝ የማስተላለፍ ሂደት ተቋርጦ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ፤ ለዚህ ምክንያቱ በመሬት አያያዝ ስረዓቱ ላይ ክፍተት እና ህገ ወጥነት ይስተዋል ስለነበር መሬት ኦዲት እየተደረገ በመቆየቱ ነው ብለዋል።
ኢዜኣ
