የተጀመሩ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያዎች በፍጥነት መጠናቀቅ እንዳለባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
የቋሚ ኮሚቴ የአገልግሎት ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢና የቡድኑ አስተባባሪ መአዛ ጥጋቤ ተቋሙ በ10 ዓመት የልማት ዕቅዱ ላይ መብራት ለሁሉም ለማድረስ እየሰራ ያለው እንቅስቃሴ እንደ ሀገር ያለው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከፍተኛ የኃይል እጥረት በመኖሩ የአካባቢውን ማህበረሰብ የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ የኃይል ማከፋፈያ ግንባታ በባህር ዳርና ከአዘዞ-ጭልጋ፣ ከባህር ዳር-ወልድያ፣ ከአዘዞ-ዳንሻ ባከር ሁመራ፣ ከባህርዳር-ቡሬ-ደብረ ማርቆስ እና ሌሎች የማስፋፊያ ስራዎች በተቀመጠላቸው እቅድ እየተፈፀሙ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በሥራ ላይ የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን በፍጥነት በመፍታት ተጠናቀው የሕዝቡን የመብራት ጥያቄ መመለስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የመብራት ኃይል ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ችግር ስላለ በ18 ወራት ለመጨረስ ውል የተገባላቸው የመብራት ፕሮጀክቶች ከ4 እስከ 5 ዓመታት ስለወሰዱ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ሕዝቡን የመብራት ተጠቃሚ የማድረግ ችግር እንዳለም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙላት ገዛኸኝ የመብራት መስመሮችን ለመዘርጋት የወሰን ማስከበር፣ ካሳ በወቅቱ የመገመት ችግርና የሲሚንቶ እጥረት ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት መሆኑን፣ ብሔራዊ ባንክ ኤሊሲ በወቅቱ ባለመክፈቱ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎችን አምጥተው ፕሮጀቶችን ለማጠናቀቅ እንቅፋት እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሰሞኑን የኤልሲ ችግር ተፈትቷል የሚል መረጃ የደረሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ካሳ የተከፈላቸው ሰዎች መነሳት ሲገባቸው በተለያየ ምክንያት ባለመነሳታቸው የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት መቸገራቸውንና ሲሚንቶ በወቅቱ አለማግኘት ለፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው የሲሚንቶ ችግርን ለመፍታትም ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር በመነጋገር ችግሩ መፍታት እንደሚቻል ጠቁመው ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ቡድኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሪፖርት በማቅረብ ክትትል እንደሚያደርጉ መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል።
ዋልታ
