ለሱዳን ሰላማዊ መፍትሄ ለማግኘት በአዲስ አበባ ውይይት ሊደረግ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም ተናገሩ።
አምባሳደሩ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት ኢጋድ ባሳለፍነው ሰኞ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሱዳን ጉዳይ ሰላማዊ መፍትሄ ለማግኘት ሁለቱን አካላት የማገናኘት ስራውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተሰጥቷል ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር በመሆን የአደራዳሪነት ሚና የምትወጣ መሆኑን ጠቁመው በሱዳን ጉዳይ ሰላማዊ መፍትሔ ለማበጀት የአራትዮሽ ስብሰባ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
ኢጋድ ከሶስት አመት በኋላ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለረዥም አመታት ሲንከባለሉ የነበሩ ጉዳዮችን እልባት የሰጠበት መሆኑንና ድርጅቱ በ50 አመት ጉዞው ታሪካዊ ሊባል የሚችል ውጤታማ ስራዎች የተሰሩበት ስብሰባ እንደነበር አንስተዋል።
ከዚህም ውስጥ በሱዳን ጉዳይ ሰላማዊ መፍትሄ ለማግኘት በትኩረት ተወያይተዋል የተባለ ሲሆን የድርጅቱ ሁሉም መሪዎች በሱዳን ሰላም የማምጣት ጉዳይ ላይ ተመሳሳይና ጠንካራ አቋም የያዙበት መሆኑ ተገልጿል።
ከሱዳን በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና ሌሎች ሀገራት የሰላም ጉዳይ ላይ መክሯል ተብሏል።
ዋልታ
